عربيEnglish

The Noble Qur'an Encyclopedia

Towards providing reliable exegeses and translations of the meanings of the Noble Qur'an in the world languages

The congregation, Friday [Al-Jumua] - Amharic translation - Africa Academy

Surah The congregation, Friday [Al-Jumua] Ayah 11 Location Madanah Number 62

1. በሰማይና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ ንጉስ፤ ፍፁም (ከጉድለት ንጹህ)፤ አሸናፊና ጥበበኛ የሆነውን አላህን ያሞግሳል::

2. እርሱ ያ ለመሃይማን ዐረቦች የቁርአን አናቅጽን በእነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፤ የሚያጠራቸዉም፤ መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸዉም የሆነን መልዕክተኛ ሙሐመድን ከእነርሱ መካከል የላከ ነው:: እነርሱም ከእርሱ በፊት በግልጽ ስህተት ውስጥ ነበሩ::

3.ከነሱም ሌሎችም ገና ያልተከተሏቸው በሆኑት ላይ የላከው ነው:: እርሱም አሸናፊና ጥበበኛ ነው::

4. ይህ የአላህ ችሮታ ነው:: ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል:: አላህ የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው::

5. የእነዚያ ተውራትን የተጫኑትና ከዚያ ያልተሸከሟት (ያልሰሩባት) ሰዎች ምሳሌ ልክ መጽሐፎችን እንደሚሸከም አህያ ብጤ ነው:: የእነዚያ በአላህ አናቅጽ ያስተባበሉት ህዝቦች ምሳሌ ከፋ:: አላህም በዳዮችን ህዝቦች አይመራም::

6. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «እናንተ አይሁዳውያን ሆይ! ከሰው ሁሉ በተለየ እናንተ ብቻ ለአላህ ወዳጆች ነን ብትሉና በዚያ አባባላችሁ እውነተኞች እንደሆናችሁ እስቲ ሞትን ተመኙ» በላቸው::

7. እጆቻቸው ባስቀደሙት ኃጢአት ምክንያት በፍጹም አይመኙትም:: አላህ በዳዮችን አዋቂ ነው::

8. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «ያ ከእርሱ የምትሸሹት ሞት እርሱ በእርግጥ አግኛችሁ ነው:: ከዚያም ሩቁንና ቅርቡን አዋቂ ወደ ሆነው ጌታ በቂያማ ዕለት ተመላሾች ናችሁ:: ትሰሩትም የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል» በላቸው::

9. እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአርብ (በጁሙዓ) ቀን ለስግደት ጥሪ በተደረገ ጊዜ ወደ አላህ ማውሳት (ኹጥባ፣ ሶላት) ተጣደፉ:: መሸጥንም ተው:: የምታውቁ ብትሆኑ ይህ ለእናንተ በጣም የተሻለ ነው::

10. ሶላቷ በተፈጸመችም ጊዜ በምድር ላይ ተበተኑና የአላህን ችሮታ ፈልጉ:: ልትድኑ ይከጀላልና አላህንም በብዙው አውሱ::

11. (መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ንግድን ወይም ዛዛታን ባዩ ጊዜም ቆመህ የተውህ ሲሆኑ ወደ እርሷ ይበተናሉ:: «አላህ ዘንድ ያለው ከዛዛታም ከንግድም በላጭ ነው:: አላህም ከሰጭዎች ሁሉ ይበልጥ ሲሳይን ሰጪ ነው» በላቸው::